ከ”ህልመኛዋ እናት” ለቅምሻ

”… ወሰድኩና እቆሻሻ ማጠራቀሚያ ላስቲኩ ውስጥ ደፍቼ ስመለስ፣ እየተንገዳገደች ወደ በሩ ስትመጣ ተገናኘን። መንገድ ለቀቅ አድርጌ፣ ዝም ብዬ አየኋት። እንደምንም እየተንገዳገደች እመፀዳጃ ቤት ደረሰችና ማስመለስ ጀመረች። እስክትመለስ በዝምታ እኮሪደሩ ላይ ቆሜ ጠበቅኋት። ግድግዳውን እየተደገፈች እንዳካሄዷ ተመለሰችና፣ በቁሟ አልጋው ላይ ዘፍ ብላ በልቧ ተኛች። ጠጥታ ነው እንዳልል ምንም የመጠጥ ሽታ አይሸተኝም። በሃዘን ልቤ ስብር እንዳለ ሁኔታዋን ቆሜ ተመለከትኳት። ፀጉሯን በሁለት እጇ ስቅስቅ አድርጋ ይዛ ትራሱ ላይ እንደተደፋች ቀረች። በአንድ ነገር እየተሰቃየች እንደሆነ ተረዳሁ።

“ትርሲት፤” አልኳት ወደ አልጋው ቀረብ ብዬ።

“ኢቮን፤ መብራቱን አጥፊልኝ እባክሽ።” አለቺኝ በጣር ድምጽ። አብረን መኖር ከጀመርን ጊዜ ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ስሜን ስትጠራ።

“ደህና አልመሰልሽኝም ትርሲት፤ እርዳታ ሳያስፈልግሽ አይቀርም፤ አንቡላንስ ልጥራልሽ?”

“እኔ ምንም አልሆንኩም። እባክሽን መብራቱን አጥፊልኝ።” አለቺኝ በልመና መልክ። …