Reviews

የተዋጣለት የትረካ እና የቋንቋ አጠቃቀም ችሎታ

ከ”የመሐረቡ ምስጢር” ለቅምሻ
ታዋቂው ጸሀፊ እና ገጣሚ ሀማ ቱማ በዚህ የእታለም እሸቴ አራተኛ የረጂም ልብወለድ መጽሀፍ ሽፋን ገጽ ላይ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል:

“በኢትዮጵያ ሰፍነው የቆዩት ሥርዓቶች በተጠቀሙት ሳንሱር፣ ባስፋፉት ኪነጥበብና አፍላቂነትን ገዳይ ቀኖና የተነሳ ስነጽሁፍ በሀገሪቱ በሚችለው ደረጃ ሊያድግ ሳይችል ቆይቷል። ደርግ በይፋ የሳንሱር ሥርዓትን አቋቁሞ፣ ቁጥጥርና አፈናውን ሲያካሂድ፣ ወያኔም ፖለቲካውን ለተከተሉ መጽሀፍትና ደራሲዎች ሜዳውን ፎገራ ሲያደርግላቸው፣ ላልፈለጋቸው ደግሞ ሁኔታውን አክብዶት ቆይቷል። እታለም በዚሁ ዘመን ብቅ ያለች የልብወለድ ደራሲ ናት። ሊሰጣት የሚገባውን አድናቆትና ዕውቅና ግን ገና አላገኘችም። መድረኩ ዛሬም በስነጽሁፍ ሰዎች ሳይሆን ፖለቲካዊ አቋሞችን በሚያጮሁ “የኪነት ሰዎች” በመያዙ ይሆናል። እታለም በመጀመሪያ በ2001 ዓ. ም. “ምንዳ” የተባለውን፣ በ 2004 ዓ. ም. “ህልመኛዋ እናት”ን፣ ለጥቃ ደግሞ በ 2008 ዓ. ም. “ተፈናቃይ ፍቅር”ን አሳትማ ለአንባቢያን አቅርባለች። እኔ እንደ እታለም የረዥም ልብወለድ ታሪኮችን ጽፌ ማቅረብ አልቻልኩም። እታለም ተራቀቅሁ፣ ከበድኩ፣ ተመጻደቅሁ በማይል ቋንቋ ከሶስት መቶ በላይ ገጾችን የሚያልፍና ከብዙኀኑ ህይወት ጋር የተሳሰረ ትረካን አስለምዳናለች። የተፈናቃዮችን ኑሮም እንኖረው ዘንድ በሚታመኑ ገጸባህርያት አማካኝነት አቅርባልናለች። በልብወለድ ጽህፈት አንዱና ዐብይ የሚሆነው ችግር የገጸባህርያቱ ቃለ-ምልልስ እውነተኛ መምሰል አለመምሰሉ ነው። ሁሉም ሲናገሩ አንድ ከሆኑ፣ የምሁሩም የገበሬውም ቋንቋ አንድ ከሆነ፣ ድርቅ ካለ መጽሀፉ ይሰለቻል። አልመስል ይላል። እታለም ግን ይህን እንቅፋት አልፋው ገጸባህርያቱ የወከሉትን ሆነው፣ የቀን ሠራተኛው ምሩቅ ፈላስፋ ሊሆን ሳይቃጣው እራሱን ሆኖ የሚቀርብ በመሆኑ የእታለም ልብወለዶች ሳይሰለቹ ይነበባሉ። ታሪኩን ይመስላሉ። አንባቢንም ይስባሉ። ይህ ደግሞ ታላቅ ችሎታ ነው። እታለም ከዘመናችን የረዥም ልብወለድ ደራሲዎች አንዷና መነበብም ያለባት ናት እላለሁ።”

ሀማ ቱማ